የስነ-ተዋልዶ ጤና
የስነ-ተዋልዶ ጤና ማለት ከተዋልዶ ጤና ጋር ተያይዞ የተሟላ የአካል፣ የስሜት፣ የአእምሮ፣ እንዲሁም የማህበራዊ ጤንነት ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የበሽታ አለመኖር ወይም የመራብያ አካላት ተገቢውን የተግባር ሂደት መተግበር መቻልን ያካትታል። ከዚህ በተቃራኒ ሁኔታ የሚገኙ ነገሮች የተዋልዶ ጤና ችግሮች ናቸው።
ለወጣቶች የተዋልዶ ጤና ትኩረት መስጠት ለምን አስፈለገ?
አብዛኞች ወጣቶች በወጣትነት የእድሜ ክልል ዉስጥ እያሉ ለተለያዩ ችግሮች በተለያዩ ምክንያቶች ይጋለጣሉ። ለእነዚህ ችግሮች በዋናነት የሚከተሉት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።
- ስለ ስርአተ ጾታእና ተዋልዶ ያሉን መረጃወች ዉስን መሆን
- የተፈጥሮ ሆርሞኖች በከፍተኛ መጠን በሰዉነታቸው ዉስጥ እየተመረቱ ስለሚሰራጩ እና በባህርያቸው እና በጸባያቸው ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩ
- የተለያዩ ነገሮችን የማወቅ፣ አዲስ ነገርን የመፈለግ ሁኔታችን ስለሚጨምር
- የህይወት አቅጣጫን የሚቀይሩ ብዙ ዉሳኔወችን የሚያሳልፉበት ወቅት በመሆኑ
- ማህበረሰቡ፣ አቻ ጓደኞች እና የሚኖሩበት አካባቢ ተጽእኖ ስለሚያደርጉባቸው እና ሌሎች መሰል ምክንያቶች ናቸዉ።
ወጣቶችን ለአባላዘር በሽታዎች የሚያጋልጡ ሁኔታዎች
- ስለ አባላዘር በሽታ በቂ ግንዛቤ ማጣት
- ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ መያዝና ግንኙነት መፈጸም
- አዘውትሮና በትክክል ኮንዶምን በትክክል አለመጠቀም
- ባጋጣሚ ካገኙት ሰው ጋር ግንኙነት መፈጸም
- በአቻ ጓደኛ ጫና ወሲብ መፈጸም
- በአደንዛዥ ዕጽ ተገፋፍቶ ወሲብ መፈጸም
- ወሲባዊ ጥቃት ለምሳሌ አስገድዶ መድፈር
የአባላዘር በሽታዎች መከላከያ ዘዴዎች
- ወሲብ መጀመርያ ጊዜን ማዘግየት(ወሲብ ላልጀመሩ)
- ከወሲብ መታቀብ(ወሲብ ለጀመሩ)
- በእያንዳንዱ የወሲብ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶምን በትክክልና ሁልጊዜ መጠቀም
- እርስ በርስ በመተማመንና በግንኙነት አብሮ መቆየት እንዲቻል ጓደኛሞች የወሲብ ግንኙነት ከማድረጋቸው በፊት ኤች አይ ቪን ጨምሮ ከአባላዘር በሽታ ነጻ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቅድመ ምርመራ ማድረግ
- በምርመራ የአባላዘር በሽታ የተገኘባቸው የጤና ባለሙያ ዘንድ መሄድና ተገቢውን ህክምና ማግኘት
- የወሲብ ጓደኛቸው በአባላዘር በሽታ መያዙን ያወቁ ወጣቶች የአባላዘር በሽታ ምልክትን ባያዩም እንኳ የጤና ባለሙያ ዘንድ መሄድና ተገቢውን ህክምና ማግኘት የመሳሰሉት ናቸው።
የወሊድ መቆጣጠሪያን በተመለከተ
የእርግዝና መከላከያ መጠቀም ለወጣቶች የሚያስገኘው ጥቅም
- ያልተፈለገ እርግዝና እና ለአደጋ የሚያጋልጥ ጽንስ ማቋረጥን ይከላከላል
- ከኤች አይ ቪ ኤድስና በግብረስጋ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ይጠብቃል(ኮንዶም)
- ወጣት ሴቶችን ከእርግዝና እና ከእርግዝናው ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ተዛማጅ የጤና ችግሮችና ሞት ይከላከላል።
- እርግዝናን እስከተፈለገው ጊዜ ያዘገያል።
- አራርቆ ለመውለድ ያገለግላል።
- ወጣት ሴት ተማሪወች ትምህርታቸውን መቀጠልና የሚመኙትን ስራ ለመፈለግ እንዲችሉ ይረዳቸዋል።
- የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ይቀንሳል።
- ወጣቶች ሃላፊነት የተሞላበት ዉሳኔ እንዲወስኑ ይረዳቸዋል።
- ወጣት ወንዶች የተዋልዶ ጤናን ሃላፊነት እንዲነጋገሩ ይረዳቸዋል።
1 ጥምር መከላከያ (dual protection)
- ጥምር መከላከያ ዘዴ ማለት እርግዝናን እና ኤች አይ ቪን ጨምሮ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎች ናቸው።
ጥምር መከላከያ ዘዴ የሚከተሉትን ያካትታል።
- ኮንዶምንና ሌላ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ በአንድ ላይ መጠቀም
- ከወሲብ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መታቀብ
- ኤች አይ ቪ የሌለባቸውና አንድ ለአንድ የተወሰኑ ጥንዶች የእርግዝና መከላከያ ዘዴን በመጠቀም ወይም ሁልጊዜ በትክክል ኮንዶምን በመጠቀም እርግዝናን እና ኤች አይ ቪን ጨምሮ በወሲብ የሚተላለፉ በሽታወችን መከላከል ይቻላል።
ከአካላዊ ቅመም (ከሆርሞን) የተዘጋጀ እርግዝና መከላከያ ዘዴ
- ጥምር አካላዊ ቅመም የያዘ እርግዝና መከላከያ እንክብል
- ነጠላ አካላዊ ቅመም የያዘ እርግዝና መከላከያ እንክብል
- በመርፌ የሚሰጥ ጥምር አካላዊ ቅመም የያዘ እርግዝና መከላከያ ዘዴ
- በመርፌ የሚሰጥ ነጠላ አካላዊ ቅመም የያዘ እርግዝና መከላከያ ዘዴ
- በላይኛው ክንድ ቆዳ ስር የሚቀበር ነጠላ አካላዊ ቅመም የያዘ እርግዝና መከላከያ(ጃዴል፣ኢምፕላኖን) ወጣት ሴቶች ከአካላዊ ቅመም የተዘጋጀ የእርግዝና መከላከያ ዘዴን መጠቀም ይችላሉ
- በማህጸን ዉስጥ የሚቀመጥየእርግዝና መከላከያ ዘዴ(ሉፕ) ከትንሽ የሚተጣጠፍ ፕላስቲክና ከመዳብ የተሰራ ሲሆን አንዳንዱ አካላዊ ቅመም(ሆርሞን) የያዘ ነው። በማህጸን ዉስጥ የሚቀመጥና እስከ 12 አመት ድረስ እርግዝናን ሊከላከል የሚችል ነው።
ዘላቂ/ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ
- በቀዶ ጥገና ዘዴ ወንዶችን ወይንም ሴቶችን ማከምን ይገልጻል። ይህ ዘዴ የሚፈልጉትን ያህል ልጆች ወልደው ለጨረሱና ወደፊት ሌላ ልጅ መውለድ ለማይፈልጉ እንጅ ልጅ ለሌላቸውና ወደፊት መውለድ ለሚፈልጉ ወጣቶች ከጊዜ በኋላ ሊጸጸቱ ስለሚችሉ ተመራጭ ዘዴ አይደለም።
ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ
- ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ ሲፈጸም ሊከሰት የሚችለውን እርግዝና ለመከላከል የሚወሰድ እንክብል ነው። ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ የሚከተሉትን ያካትታል።
- የአስገድዶ መደፈር ችግር ሲያጋጥም
በወሲብ ወቅት ምንም አይነት የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ሳይጠቀሙ ሲቀር
የእርግዝና መከላከያ ዘዴውን በትክክል ሳይጠቀሙ ሲቀር
ለምሳሌ ፥ በወሲብ ግንኙነት ወቅት ኮንዶም ቢሾልክ ወይም ቢቀደድ፣ ከእርግዝና ነጻ የሚሆኑበት ቀን አቆጣጠር ላይ ስህተት ቢፈጠርና በዚህ ወቅት ወሲብ ቢፈጸም፣ የወንድ የዘር ፍሬ ከሴት ብልት ዉጭ በማፍሰስ እርግዝናን ለሚከላከሉ የወንድ የዘር ፍሬ ከውጭ ማፍሰስ ሲያቅት።
ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ እንደተፈጸመ ቢቻል ወዲያው ቢወሰድ ያልተፈለገ እርግዝናን የመከላከል እድሉ ከፍተኛ ነው። አልያ ደግሞ እስከ አምስት ቀን ውስጥ መወሰድ አለበት።
ያልታቀደ እርግዝና
ያልተፈለገ እርግዝና ማለት ወጣት ሴት በአካል፣በስነልቦና፣በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ ህይወቷ ልጅ ለመውለድና ለማሳደግ ዝግጁ ሳትሆን ሳትጠብቀው የሚፈጠር እርግዝና ሲሆን ቤተሰብም ሆነ ማህበረሰቡ የማይቀበሉት እርግዝና ነው። ወጣቶች የእርግዝና መከላከያ ሳይጠቀሙ ወሲብ ቢፈጽሙ ላልተፈለገ እርግዝና ሊጋለጡ ይችላሉ።
ያልታቀደ እርግዝና መንስዔዎች
ከግንዛቤ ማጣት የተነሳ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን አለመጠቀም
ስለ እርግዝና መከላከያ ዘዴዎች ያለ የተሳሳተ አመለካከት
የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ አለመጠቀም
ከወሲብ ጓደኛ ጋር ስለ ወሲብ ግንኙነት በግልጽ አለመወያየት
ወሲባዊ ስሜትን ባለመቆጣጠር ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ መፈጸም
በወሲብ ጊዜ የኮንዶም መቀደድ ወይም መሹለክ
በእያንዳንዱ የወሲብ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶምን ከመጠቀም መዘናጋት
እርግዝና መችና እንዴት እንደሚከሰት ባለመገንዘብ ወሲብ መፈጸም
በወጣትነት ዕድሜ (ከ18 ዓመት በታች) የሚደረግ ጋብቻ
በሴቶች ላይ የሚደርስ ተጽዕኖ ለምሳሌ አስገድዶ መድፈር…..
ያልተፈለገ እርግዝና የሚያስከትላቸው ችግሮች
- ትምህርት ማቋረጥ
- የወደፊት ህይወት መበላሸት
- ከቤተሰብ እንክብካቤ በማጣትና በመገለል ከቤት መባረር
- በቤተሰብና በማህበረሰቡ መገለል
- ከቤት በመውጣት ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር
- በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ወደ ሴት አዳሪነት መግባት
- ጽንሱን ለማስወረድ ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ ማካሄድ
ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ የሚያስከትለው መዘዝ
- እስከ ሞት የሚያደርሱ የተለያዩ የጤና ችግሮች(የምጥ መርዘም፣ የደም መፍሰስ፣ከፍተኛ የደም ግፊት ወዘተ)
የስነልቦና ቀውስ(እራስን እስከማጥፋት)………
ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል
- ላልተፈለገ እርዝና ሊያጋላጡ የሚችሉ ባህርያትን ለማስወገድ የህይወት ክህሎትን ማዳበር
- ስለ እርግዝና ያለን ግንዛቤ ማዳበር : ወጣቶች ስለ ወንድ/ሴት የመራቦ አካላት ቅንጅታዊ ተግባራት፣የወር አበባ ዑደት ፣እንዲሁም
- እርግዝና እንዴትና መች እንደሚከሰት በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል።
- የእርግዝና መከላከያ ግንዛቤን ማዳበርና የእርግዝና መከላከያ መጠቀም
- ያልታቀደ ወሲብ በተፈጸመ ጊዜ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴን መጠቀም…….